Psalms 64

የተሳዳቢዎች ቅጣት

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1አምላክ ሆይ፤ የብሶት ቃሌን ስማ፤
ሕይወቴንም ከሚያስፈራ የጠላት ዛቻ ከልላት።

2ከክፉዎች አድማ ሰውረኝ፤
ከዐመፀኞችም ሸንጎ ጋርደኝ።
3እነርሱ ምላሳቸውን እንደ ሰይፍ ይስላሉ፤
መርዘኛ ቃላቸውንም እንደ ፍላጻ ያነጣጥራሉ።
4አሸምቀው ንጹሑን ሰው ይነድፉታል፤
ድንገት ይነድፉታል፤ አይፈሩምም።

5ክፉ ተግባር ለማከናወን እርስ በርስ ይመካከራሉ፤
በስውር ወጥመድ ለመዘርጋት ይነጋገራሉ፤
“ማንስ ሊያየን ይችላል?”
ወይም ማንስ ሊያያቸው ይችላል
ይባባላሉ።
6ግፍን ያውጠነጥናሉ፤
ደግሞም፣ “የረቀቀች ሤራ አዘጋጅተናል” ይላሉ፤
አቤት! የሰው ልቡ፣ አእምሮውም እንዴት ጥልቅ ነው!

7እግዚአብሔር ግን በፍላጻው ይነድፋቸዋል፤
እነርሱም ድንገት ይቈስላሉ።
8በገዛ ምላሳቸው ያሰናክላቸዋል፤
ጥፋትንም ያመጣባቸዋል፤
የሚያዩአቸውም ሁሉ በትዝብት ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።

9የሰው ልጆች ሁሉ ይፈራሉ፤
የእግዚአብሔርን ሥራ በይፋ ያወራሉ፤
ያደረገውንም በጥሞና ያሰላስላሉ።

10ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይበለው፤
እርሱንም መጠጊያ ያድርገው፤
ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው።
Copyright information for AmhNASV